Ethiopian Diaspora community in Germany.

Ethiopian Diaspora community in Germany.

NO ONE IS FREE UNTIL ALL ARE FREE

በርሊንም እንደ አምቦ ተቀወጠች ! (ከ ኆኅተብርሃን ጌጡ)

ከትዉልድ ወደ ትዉልድ፤ ዘለዓለም ከምናይ እኩይ፤

በግላጭ የነገን ሠላም ሕልም እንይ።….

ይለናል በተባ ብዕሩ ፀሐፊዉ የምሥጢረኛዉን ባለቅኔ የፀጋዬ ገብረ መድኅንን ሥራዎች በማጣቀስ። አዎ, ኢትዮጵያዉያን ሕልም አላቸዉ። ገና ያልተተረጎመ፤ በሥራ ላይ ያልዋለ ፍቺ አልባ ሕልም። ለዘመናት ዕንቆቅልሽ የሆነ ሕልም። ትናንትም፤ ዛሬም ዕንቆቅልሽ? በ 1953 የታለመዉ ሕልም የመሄጃዉና የመዳረሻዉ አቅጣጫ በዉል እንኩዋ ባይታወቅም፤ ሳይጀመር ጨነገፈ። የ 1966 ቱ ደግሞ ሕልሙ ድርጅት አልባ ሆኖ ኖሮ፤ በብረት የተደራጀዉ ነጠቀዉና ሕልሙንም በብረት ፈታዉ። 17 ዓመት አርግዞ የነበረዉም ሕልም በ 1983 ሽፍቶች ከጫካ መጡና ዘረፉት (ነጠቁት)። ይህም ዘረፋ ይኸዉ እስካሁን ለ 27 ዓመት እንደቀጠለ ነዉ።

ለመሆኑ ሕልሙ ምንድነዉ? አጭርና ግልፅም ሕልም ነዉ። በኢትዮጵያ ምድር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይፈጠር ነዉ። ለሁሉም ዜጋ እኩል የሆነች የእኛ የምንላት አገር ትኑረን ነዉ? እኔ ብቻ አዉቅልሻለሁ የሚል የፖለቲካ ቡድን አካል ብቻ አካኪ ዘራፍ እያለ የሚያቅራራባት የግሉም ያደረጋት ዘመን አክትሞ ለሁላችንም የሆነች አገር ለምን ግን መፍጠር አልተቻለም ነዉ ጥያቄዉ? ሌላዉን ሁሉ ሙከራ እንተወዉና በ 1997 እንደገና ተሞከረ። አሁንም ጨነገፈ። ኮሎኔል ደመቀን ተመስሎ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት እንደገና ሕልም ታዬ። ሕልሙን ግን አሁንም ገና በተግባር መተርጎም አልተቻለም። ሥርዓቱ ግን በጠና ታሟል። የፃዕረ ሞት ትግል በማድረግ ላይም ይገኛል። ነፍስ ዉጪ ነፍስ ግቢ። ፈዉሱም የመሠረታዊ ለዉጥ እንክብል መዋጥ ብቻ መሆኑ ይታመናል። ብዙ የፖለቲካዉ ዓለም ጠበብቶችም ይህን ሐቅ ይናገራሉ። በሽተኛዉ አካል ግን የዕድሜ ማራዘሚያ እንክብል መዉሰድ ብቻ እንጂ፤ የለዉጥ ፈዉስ መድኃኒቱን ሊዉጠዉ ከቶዉኑ አልፈለገም። እናም የዕድሜ ማራዘሚያ የአስቸኩዋይ ጊዜ አዋጅ እንክብሉን ለ 6 ወር ለመዉሰድ ተዘጋጅቷል።

ሕዝቡ ይህን እርምጃዉን ለመቀበል ግን ፈቃደኛ ሆኖ አልተገኘም። በአዋጁ ማግሥትም እስኪ ምን ታመጣለህ? ብሎ በየከተማዉ በቤት ዉስጥ አድማ ቀወጠዉ። ሱቆች ሁሉ ክርችም ተደርገዉ ተዘጉ። ጎዳናዎች ሁሉ ባዶ ሆኑ። አራት ጎማም፣ ሁለት አግርም ጭራሽ በከተማዉ ዝርዉ አይልም። የያንዬዉ ዘመን ትዉልድ እንደገና ተፈጠረ። ማን ይፈራል ሞት እያለ እየዘመረ፤ በሕይወቱ ቤዛነት ነፃነቱን ሊያዉጅ ወሰነ። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሀገሩ ምድር አብቦ እንዲፈካ ከመሠረታዊ ለዉጥ ባሻገር ስለቱ ወደ ሀፎቱ እንደማይገባ አስረግጦ በድፍረት ተናገረ። በተግባርም አረጋገጠ። ሕዝባዊ አመጹ ቄሮና ፋኖን አማጠና ወለደ። አሁን ደግሞ ዘርማ ተቀላቀለዉ። ጉልበቱ እየፈረጠመ ሄደ። ከዓመታት በፊት ለእስር ተዳርገዉ የነበሩት እስረኞች ከእስር ሲፈቱ እልፍ አእላፍ ሆነዉ ወጡ። ዓላማቸዉን የሚያራምድ ትዉልድ ተቀላቀላቸዉ። ከጎናቸዉ ተሰለፈ። ሞራላቸዉን ገነባዉ። ብቻችሁን አይደላችሁም አላቸዉ።

ዲያስፖራዉም በየሚኖርበት አገር ይህንኑ እርምጃ ተከተለዉ። ከወገኑ ጎን ቆመ። ሞቱን በአካል ባይጋራም፤ የወገኑ ደም ደሙ መሆኑን፤ ኤሎሄ፤ ኤሎሄ እያለ በየአደባባዩ ድምጹን ከፍ አድርጎ አስተጋባ። የሰሞኑ የበርሊኑ ሠላማዊ ሰልፍ ዓላማም በይዘቱ ከዚሁ ጋር የተቆራኘ ነዉ። የሰልፉም ቀን ደረሰና የጀርመን አገር ኗሪ ኢትጵያዉያን ሁሉ ወደ በርሊን ጎረፉ። በየብስ፣ በአየር ሁሉም እንደሚያመቸዉ ወደ በርሊን ተመመ። ሌሊቱን ሲጉዋዙ አድረዉ በተባለዉ ሰዓት ከተፍ አሉ። ከደቡብ፤ ከስሜን፤ ከምዕራብ፤ ከምሥራቅ፤ ከመሀል ጀርመን የቀረ ኢትዮጵያዊ አለ ብሎ መናገር ያስቸግራል። የኪሎ ሜትር ርቀት አላገዳቸዉም። ጆሮ የሚጠብሰዉን የአዉሮፓዉን የክረምት ብርድም አልፈሩትም። ካቦርቱን ደራረቡበት። ሳይመነኩሱ በእራስ ቅላቸዉ ላይ ቆቡንም ጫኑበት። የእጅ ጉዋንቱንም አጠለቁት። ብርድ ተከላካዩን የክረምት ጫማም ተጫሙት። ቁር በአጠገባቸዉ ድርሽ ማለት አልቻለም። እንደ ቆምጫምባዉ ለጎሪጥ እያያቸዉ አለፈ። በዓይናቸዉ የሚታያቸዉ በከንቱ የሚፈሰዉ የወገናቸዉ ደም እንጂ፤ የክረምቱ ወራት ብርድ አይደለም። እርስ በርስ ሲተራረቡ ጥርስ አያስገጥሙም። አንዱ ብርዱን ሲያማርር፤ ሌላኛዉ ይሰማና፤ ዝም በል! አሁን ይኸ ብርድ ከፌዴራል ጥይት ይብሳል? በመባባል እግረ መንገዳቸዉንም የሀገር ቤቱ ወገናቸዉ ያለበትን ሁኔታ በመግለፅ መልክት እያስተላለፉ ይጎነታተላሉ።

እንዲህ እንዲህ እየተባባሉ የሰልፉ ሰዓት ደረሰና ልብሰ ተክህኖ በለበሱ የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖት አባቶች ሥርዓተ ጸሎት ተባረከና ሰልፉ ተጀመረ። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ችግሩ ተሰምቶት በነቂስ መጥቷል። ምንም እንኩዋ የስደትን ዕድሜ ማወቅ ቢከብድም (ሰዉ ወደ ዉጭ ሲወጣ እንደገና ክርስትና ስለሚነሳ)፤ በዕድሜ የአኃዝ ሰንጠረዥም ከወጣት እስከ አረጋዊ የቀረ ያለ አይመስልም። አረንጉዋዴ፤ ቢጫ፤ ቀይ ኅብረቀለም ያለዉን ሰንደቅ ዓላማችንንም ሳይዝ የመጣ ሰዉ አልነበረም። ይህ ደግሞ ሰልፉን የበለጠ አደመቀዉ። በህብረ ቀለም አስዋበዉ። ምን አለፋችሁ! ያለማጋነን በርሊን ከኢትዮጵያ ከተሞች አንዷን መስላ ዋለች። ለሠልፉ በወጣዉ መርኃ ግብርም መሠረት ከጀርመን ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንስቶ በብዛት የተለያዩ መሥሪያ ቤቶችና የቱሪስት መናኻሪያነት በታወቁ አደባባዮች እየተመመ አለፈ። በሰልፉ አዘጋጅ ኮሚቴ የተዘጋጀዉ ደብዳቤ የመጀመሪያዉ በዉጭ ጉዳይ ሚ/ር የምሥራቅ አፍሪካ ተወካይ ለሆኑት ለሚስተር Matthias Dehner በእጅ እንደተሰጠ የኮሚቴዉ ተወካይ የሆኑት አቶ አፈወርቅ ተፈራ ለዚህ ዘገባ ዝግጅት ገልጸዋል። አያይዘዉም ይኸዉ የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር የምሥራቅ አፍሪካ ተወካይ …የኢትዮጵያን ጉዳይ ሀገራቸዉ በቅርብ እንደምትከታተልና በቅርቡም የወጣዉን የአስቸኩዋይ ጊዜ አዋጁን አስመልክቶ መግለጫ እንዳወጣችና በብሔራዊ መግባባትና በዉይይት ችግሩን መንግሥት መፍታት እንዲችል ማሳሰባቸዉን መግለጻቸዉን ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ፤ የሰልፉ የልዑካን ቡድን ጀርመን ያወጣችዉ መግለጫ በጣም የተለሳለሳና በአሁኑ ጊዜ ሀገራችን ኢትዮጵያ ካለችበት ችግር አንፃር ያላረካቸዉ መሆኑን በእሰጥ አገባ እንደሞገቷቸዉ አክለዉ ገልጸዋል። ያልተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓትና የአስቸኩዋይ ጊዜ አዋጅ ላወጀ መንግሥትም ስደተኞችን በሀገሩ ዜጋ ላይ ግፍና ሰቆቃ እየፈጸመ ለሚገኝም መንግሥት አሳልፎ ለመስጠት መዘጋጀት የሰብዓዊ መብት መከበር ቆሜያለሁ ከሚል እንደ ጀርመን ላለ መንግሥት የማይጠበቅና አሳፋሪ ድርጊት እንደሚሆንም በመግለጽ ከእንዲህ ዓይነት እርምጃ አወሳሰድ ዉሳኔ መንግሥታቸዉ እንዲቆጠብ በደብዳቤያቸዉ ማሳሰባቸዉንም አክለዉ አስገንዘበዋል።

ይኸዉ ሰልፉን አስመልክቶ በጀርመንኛ እና በእንግሊዘኛ የተዘጋጀዉ ደብዳቤ (ጽሁፍ) ለጀርመን ካንሰለር ለ ዶ/ር አንጄላ ሜርክል፤ ለጀርመን ቡንደስታግ ቢሮ ለ ዶ/ር ወልፍጋንግ ሾይብለ፤ ለአዉሮፓ ኮሚሽን የጀርመን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት መሰጠቱን የሰልፉ አዘጋጅ ኮሚቴ አስታዉቁዋል። የደብዳቤዎቹ አጠቃላይ ይዘትም፤በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን በኢትዮጵያ ለሚታየዉ ችግር መንግሥት ያወጀዉ የአስቸኩዋይ ጊዜ አዋጅ መፍትሔ ማምጣት እንደማይችል፤ ሀገሪቱ ወደ ባሰ አዘቅት ከመግባቷ በፊት ሠላማዊ ሽግግር እንዲደረግ ጀርመን የበኩሏን የዲፕሎማሲ ጫና እንድታደርግ፤ እራሷ እንደ ሀገርና በአዉሮፓ ሕብረትም ዉስጥ ባላት ቦታ ይህንኑ ሚና እንድትጫወት የሚያሳስብ ጠንከር ያለ ደብዳቤ እንደሆነ የኮሚቴዉ አባላት ለሰላማዊ ሰልፈኛዉ በሰልፉ የማጠናቀቂያ ፕሮግራም ላይ በየተራ ባደረጉት ንግግር አስታዉቀዋል። ለሚመለከታቸዉ መሥሪያ ቤቶች ከተዘጋጀዉና ከተሰጠዉ ደብዳቤ በተጨማሪ ሰልፈኛዉ ባለፈባቸዉ አዉራ ጎዳናዎች ግራና ቀኝ ሰልፉን በመገረም ይመለከት ለነበረዉ ሕዝብም እንዲሁ የተዘጋጁ በራሪ ጽሁፎች በብዛትና በበቂም ተበትነዋል (ተሰራጭተዋል)። ይዘታቸዉም ባጭሩ ሕዝቡ የሚከፍለዉ ታክስ አለአግባብ በእርዳታ ሥም ለአምባገነኖችና የራሳቸዉን ዜጋ ለሚገሉ ነፍሰ ገዳዮች መዋል ስለሌለበት፤ ሕዝብ ባገኘዉ አጋጣሚ ሁሉ መንግሥታቸዉን መጠየቅ እንደሚገባዉ የሚያስገነዝቡ መሆናቸዉን የሰልፉ አዘጋጅ ኮሚቴ አስረግጦ ተናግሯል። በተለይም ደግሞ ሰልፉ የተካሄደባቸዉ ሥፍራዎች በብዛት ሕዝብ የሚያዘወትራቸዉ፤ የቱሪስት መናኻሪያ የሆኑ ቦታዎች፤ የኤምባሲ ጽ/ቤቶች ለምሳሌ እንደ (የአሜሪካ፤ የእንግሊዝ፤ የፈረንሳይ፤ የራሽያ ወዘተ …. ) የመሳሰሉ በመሆናቸዉ ደብዳቤዎቹን በብዛት ለማሰራጨት ተችሏል። ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስከ ቀድሞዉ …… ራይሽታግ … ሕንፃ (የአሁኑ ቡንደስታግ) ከዚያም እስከ ካንሰለሯ ቢሮ ድረስ ከ 5 ኪሎ ሜትር ያላነሰ የእግር ጉዞ ስለነበር በነዚህ መንገዶች ግራና ቀኝ ለተገኘዉ መንገደኛ ሁሉ በራሪ ወረቀቶቹን ማደል ተችሏል።

የአሁኑ በርሊን ላይ የተደረገዉ ሠላማዊ ሰልፍ በብዛትም ሆነ፤ በአቀነጃጀት የደመቀና የተዋጣለት ነበር ማለትም ይቻላል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ጀርመን አገር የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ የሲቪክ ተቁዋማት፤ አብያተ ክርስቲያናት፤ የእስልምና እምነት ተከታዮች፤ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲዎች፤ በአጠቃላይ የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል፤ ይመለከተኛል የሚል ሁሉ ከግለሰብ እስከ ተቁዋም የተማከለበት የሰልፉ አዘጋጅ ኮሚቴ በጀርመን ደረጃ በማዋቀር በቂ ቅስቀሳና ቅድመ ዝግጅት በተቀናጀ መልክ ማካሄድ ተችሏል። ማቄን ጨርቄን የሚል ዓይነት ምክንያት እየፈጠሩ እራስን ለማግለል ካልተፈለገ በቀር እኔን አይመለከተኝም የሚያስብል ምክንያት በሰልፉ ዝግጅት አልታዬም።ይህም በመሆኑ ምክንያት የጀርመን አገር ኗሪ ኢትዮጵያዉያን በራሳቸዉ ሀገራዊ ስሜት ተነሳስተዉ ያደረጉት ሰልፍ ስለነበር ዉጤቱም የተሳካ መሆን ችሏል። የጨሰም፤ እንዲነድ፤ የደመነም እንዲዘንብ ከተፈለገ ከእግዜአብሔር ምሕረት መዉረድ ጋር የእኛም መተባበር እጅግ አስፈላጊ ነዉና የበርሊኑ የሰላማዊ ሰልፍ ትብብር ለወደፊቱም በተጠናከረ መልክ ቀጥሎ ዓላማችን እንዲሳካ አንድነታችንን ማጠናከር ግድ ይላል።

ይህን ሠላማዊ ሰልፍ ለየት ያደረገዉ ሌላዉ አስገራሚ ጉዳይ ደግሞ በሰልፉ ማጠቃለያ ላይ ለሰልፈኛዉ በቅርቡ ከእስር የተፈታዉ አንዱዓለም አራጌ በስልክ ያስተላለፈዉ መልክት ነዉ። እንደሚታወቀዉ ወጣት አንዱዓለም አራጌ በሀገራችን ዲሞክራሲና ነፃነት፤ ብሎም የፍትሕ ሥርዓት እንዲሰፍን በመታገሉ ብቻ በአገዛዙ እንደ አሸባሪ ተቆጥሮ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት ለ 6 ዓመታት ያህል በእስር ቆይቶ ሰሞኑን በጎርፉ ምክንያት ተፈቷል።ይኸዉ … ያልተሄደበት መንገድና .. የሀገር ፍቅር ዕዳ.. የተሰኙ ሁለት መፃሕፍት ደራሲና ወጣት ታጋይ፤ የምንፈልገዉን ዓላማ ለማሳካት የዲያስፖራዉም ሚና ቀላል አለመሆኑን በመግለፅ በሰከነ መንገድ ይህን የዘረኝነት ሥርዓት ለማስወገድ እና የምንፈልገዉን የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመፍጠር ሁሉም አሻራዉን እንዲያስቀምጥ በአፅንኦት የሰልፉን ታዳሚ አስገንዝቧል።

ከሰልፉ አዘጋጅ ኮሚቴዉ ገለፃ ለመረዳት እንደተቻለዉም፤ ሠላማዊ ሰልፉ የተካሄደዉ ቀደም ሲል ከሁለት ወር በፊት በተያዘ ፕሮግራም መሠረት ነው። በመሀሉ ሁለት አስገራሚ ክስተቶች በሀገራችን ተፈፅመዋል። ሁሉም ባይሆኑ በከፊል እስረኞች ተፈተዋል። ለ6 ወር ያህል የሚቆይ የአስቸኩዋይ ጊዜ አዋጅ ታዉጇል። እነኝህ ሁለት ክስተቶች ደግሞ ይበልጥ ሠላማዊ ሰልፉ እንዲደረግ ጫና ማሳደራቸዉንም አዘጋጅ ኮሚቴዉ ሳይገልጸዉ አላለፈም። ምንም እንኩዋ እስረኛ መፍታት ወይም ለእስረኛ ምህረት ማድረግ ከተጠየቀዉ መሠረታዊ ጥያቄ አንፃር የማይመጣጠን እርምጃም ቢሆን፤ በእሥረኞቹ መፈታት ለእስረኞቹ ለእራሳቸዉና ለቤተሰቦቻቸዉ ሰልፈኞቹ ደስታቸዉን ገልጸዋል። ያለ ኃጢአታቸዉ ተፈርዶባቸዉ ሲኦል ወርደዉ የነበሩ እስረኞች ወጥተዉም ለገነት ባይታደሉም፤ ከቤተሰባቸዉ መቀላቀል መቻላቸዉ እንደ ሰብዓዊ ፍጡር አስደሳች ዜና መሆኑ ደግሞ ሊካድ አይገባዉም። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በአስቸኩዋይ ጊዜ አዋጁ ደግሞ ተቃዉሟቸዉን አሰምተዋል።

ከተነሳዉ ሕዝባዊ ተቃዉሞ አንፃር ተጠብቆ የነበረዉም፤ ብሔራዊ መግባባትና ብሔራዊ እርቅ እንጅ፤ ብሔራዊ እስር ቤት ማዘጋጀት አልነበረም። በበር ከእስር ቤት ፈቶ በመስኮት እንደገና ለማስገባት ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ሰይጣናዊ ተግባር እንጂ፤ ለሠላም መዘጋጀትን አያመለክትም። ከእስር የተፈቱት እስረኞች እራሳቸዉ ያነሳነዉ ጥያቄ ሳይመለስ እኛ ግን በደፈናዉ ከእስር ተፈተናል። ይህ እርምጃ ግን መፍትሔ አይደለም። ሁሉም ነገር የሀገራችን ጉዳይ ዛሬም እንደ ትናንቱ እንቆቅልሽ ነዉ እያሉ እየተናገሩ ነዉ። እንቆቅልሹን ማን ይፍታዉ? የንግሥት ይርጋን አገላለፅ ልዋስና ማዕከላዊም ሆነ የተለያዩ እስር ቤቶችን ብዙ ከመናገር በደፈናዉ … የምድር ሲኦሎች… ብሎ ማለፉ ይቀላል ትላለች። ግን የሚፈለገዉ መሠረታዊ ለዉጥ በሀገራችን እስካልመጣ ድረስ አሁንም ግድያ መፍትሔ መሆን አይችልም። ሲኦል ተብለዉ በሚጠሩት እስር ቤቶችና ዉጭም ባለዉ ሕይወትመኖር መካከል ልዩነቱ ስላልታየ፣ ትዉልዱ ኖርንም፤ ሞትንም አንድ ነዉ! እየታገልን እንሞታለን ብሎ ወስኗል። ከመሠረታዊ ለዉጥ ባሻገርም ሌላ አማራጭ ሁነኛ መፍትሔ አይታይም።

ዲያስፖራዉ በሀገሩ ብሩህ ተስፋ እንዲኖር ይፈልጋል። በወገኑ በከንቱ ደም መፍሰስ ይቆጫል። ወንድማማቾች እርስ በርስ ሲፋጁ ያዝናል። ሥልጣን የአንድ ሀገር ሕዝብ የመገልገያ መድረክ እንጂ፤ የእርስ በርስ መፋጃ መሣሪያ ሲሆን ልቡ ይደማል። በተለይም ደግሞ በየሚኖርበት አገር የሚያየዉን፤ የሚኖረዉን ሕይወት ከሀገሩ የፖለቲካ ሥርዓት ጋር እያነፃጸረ መቼ ይሆን እኛ እንዲህ ዓይነት ሥርዓት የሚኖረን እያለ ከእራሱ ጋር ይሟገታል። በሰሞኑ የበርሊኑ ሠላማዊ ሰልፍ መነሻነት፤ ይህን ጥያቄ የማይጠይቅ የጀርመን አገር ኗሪ ኢትዮጵያዊ የለም። ወደ 5 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ሰልፍ በበርሊን መሀል አደባባዮች ያ ሁሉ ሰዉ በእግሩ ሲተም የመኪና መንገዶች ለትራፊክ ዝግ ናቸዉ። ያዉም በሰዉ አገር።

ፖሊሶች ሰልፉን ከፊት ለፊት ይመራሉ። ከሁዋላም አጅበዋል። ሕዝቡ ግራና ቀኝ በአንክሮ ይመለከታል። …ኦሮሞ ኬኛ… የሚለዉ የድምፀ መረዋዉ የመሀሪ ደገፋዉ ሙዚቃ አደባባዩን ሲያድልቀልቀዉ ደግሞ፤ አብረዉ ዉዝዋዜዉን ተያያዙት። አብረዉ ሙዚቃዉን አቀለጡት። ለካስ ሙዚቃ እራሱ ቁዋንቁዋ ነዉ። ትርጉም አያስፈልገዉም። አንድም ታጣቂ ፊዴራል አላየንም። ሥነ ሥርዓት አስከባሪ፤ ሰልፍ አድራጊዉን ሕዝብ ጠባቂ እንጂ። እንዲህ ዓይነት ሥርዓት በሀገራችን መቼ ይሆን የሚሰፍነዉ እያለ እራሱን የማይጠይቅ ሰልፈኛ አልነበረም። ያስቀናል። ይህን የበርሊንን ሠላማዊ ሰልፍ ሁኔታ ስንገልፅ፤ የበርሊን ኗሪ ኢትዮጵያዉያንን፤ የነ በላይ ተሾመን መስተንግዶ ሳይጠቅሱ ማለፍ የእጃቸዉ አመድ አፋሽ መሆን ነዉና ያ- እንዳይሆን፤ ቃላት በማይገልጸዉ መንገድ ለነበረዉ መስተንግዷቸዉ ምስጋናችን ይድረሳቸዉ። ጊዜው ወርኃ ጾም ባይሆን ኖሮ አንኩዋ ፍሪዳ ለመጣልም አንታማም ነበር ባዮች ናቸዉ በርሊኖች።